የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በቀጣይ ዙር እንደሚሰጥ የሀገር ዐቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግኽምራ ዞኖች በሁለተኛ ዙር ፈተና የሚሰጥባቸው አካባቢዎች ናቸው ብለዋል።

ከ90 በመቶ በላይ ተፈታኞች በመጀመሪያው ዙር ፈተናቸውን ይወስዳሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ “በሁለተኛው ዙር ፈተና የሚወሥዱ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ግንባታና ክለሣ ተደርጎ ፈተና ይወሥዳሉ” ብለዋል።

በአማራ ክልል ግጭት አለባቸው ተብለው ከተለዩት ውጪ ተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች የሚለዩ ቦታዎች ካሉ በ2ኛው ዙር ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሏል።

በዚህ አመት ከ600 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከ2 ሺሕ በላይ በሆኑ የፈተና ጣቢያዎች ለመፈተን ተመዝግበዋል።