ትምህርት ሚኒስቴር Input Output HK Limited (IOHK) ከተባለ አለም አቀፍ ተቋም ጋር ለተማሪዎች እና መምህራን ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችለው ፕሮጀክት ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከ IOHK ዋና ስራ አስኪያጅ ቻርለስ ሆፕ ጋር ተፈራርመዋል፡፡በ 3680 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ላሉ 5 ሚሊየን ተማሪዎች እና 750 ሺህ መምህራን የትምህርት ሚኒስቴር የዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ከ IOHK ጋር ከዚህ ቀደም ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል፡፡የአሁኑም ስምምነት የ መጀመሪያው ዙር በመጠናቀቁ ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ በመገምገም በታሰበለት ደረጃ እና በሚጠበቀው ጊዜ ለማድረስ ያለመ ነው ተብሏል፡፡በስምምነቱ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፕሮጀክቱ በታሰበው ደረጃ መሄዱን አድንቀው በስምምነቱ መሰረት የ መጀመሪያው 1 ሚሊየን የዲጂታል መታወቂያ በዚህ አመት መጨረሻ ለተማሪዎች እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡የ IOHK ዋና ስራ አስኪያጅ ቻርለስ ሆፕ በበኩላቸው ድርጅታቸው ዲጂታል መታወቂያውን በስምምነቱ መሰረት በተያዘው ጊዜ እንደሚያስረክቡ ገልፅው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቀጣይነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡የተማሪዎች እና መምህራን ዲጂታል መታወቂያ የትምህርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡